የቀደመ የወንጀል ጥፋተኛነት እንደ ጠቅላላ የቅጣት ማክበጃ የሚያገለግልበት ሁኔታ ከኢትዮጵያ የወንጀል ሕግ አንፃር ሲገመገም (Assessment of Prior Criminal Conviction as A General Penalty Aggravating Factor Under the Criminal Code of Ethiopia)

  • ዶ/ር ደጀኔ ግርማ ጃንካ
Keywords: ወንጀል፣ ጥፋተኛነት፣ ቅጣት፣ የወንጀል ሪከርድ፣ የቅጣት ማክበጃ፣ የቅጣት ማቅለያ

Abstract

በአንድ ማህበረሰብ ውስጥ ሠላም፣ ደህንነት እና መረጋጋት እንዲኖር ለማድረግ ከሚያስፈልጉ መሰረታዊ የሕግ ማዕቀፎች መካከል አንዱ የወንጀል ሕግ ነው፡፡ የወንጀል ሕግ ሰዎች መፈፀም የማይገባቸውን ድርጊቶች እና ማከናወን የሚገባቸውን ተግባራት በዝርዝር የሚደነግግ ሲሆን ድንጋጌው ሳይከበር ሲቀር ጥፋተኞቹ እንዲቀጡ ያዝዛል፡፡ በተፈፀሙ ወንጀሎች ምክንያት በጥፋተኞች ላይ የሚጣሉ ቅጣቶች በተጣሱ ድንጋጌዎች መሰረት የሚለዩ ሲሆን እንደ ሁኔታው እነዚህ ቅጣቶች ሊቀሉ ወይም ሊከብዱ ይችላሉ፡፡ በኢትዮጵያ የወንጀል ሕግ መሰረት ቅጣት እንዲከብድ ከሚያደርጉ ሁኔታዎች መካከል አንዱ የቀደመ የወንጀል ታሪክ/ሪከርድ ነው፡፡ ነገር ግን የቀደመ የወንጀል ሪከርድ መኖሩ በቀጥታ ያለ አንዳች ቅድመ ሁኔታ ቅጣት እንዲከብድ የሚያደርግ ሁኔታ ሳይሆን አስፈላጊ የሆኑ መስፈርቶች ተሟልተው ሲገኙ ብቻ ቅጣት የማክበድ ውጤት ይኖረዋል፡፡ በዚህ ፅሁፍ ውስጥ የተቃኘው ጉዳይም ከሀገራችን የወንጀል ሕግ አንፃር የአንድ ሰው የቀደመ የጥፋተኛነት ታሪክ/ሪከርድ እንደ ጠቅላላ የቅጣት መክበጃ የሚያገለግለው መቼ ነው የሚለው ነጥብ ነው፡፡ ይህን ጥያቄ ለመመለስ የተለያዩ የህትመት ስራዎች ዳሰሳ በማድረግ የወንጀል ሪከርድ ትርጉም እና ውጤቱ ምን እንደሆነ ታይቷል፤ የተለያዩ ሀገሮች ልምድ ተቃኝቷል፤ ተገቢነት ያላቸው የሀገራችን የወንጀል ሕግ ድንጋጌዎች ተተንትኗል፤ በጉዳዩ ላይ የሕግ ባለሙያዎች ሀሳብ እንዲሰጡበት ተደርጓል፤ በፍ/ቤት የተሰጠ ውሳኔንም ለመጠቀም ተሞክሯል፡፡ በዚሁ አግባብ ፅሁፉ የቀደመ የወንጀል ሪከርድ/ታሪክ እንደ ጠቅላላ የቅጣት ማክበጃ ሊያገለግል የሚችለው ጥፋተኛው ቀድሞ በተጣለበት ቅጣት መሰረት የመማር እድል አግኝቶ በዚህ ዕድል በመጠቀም ሳይማር ከቀረ እና ሌላ ወንጀል ፈፅሞ ከተገኘ ብቻ ነው የሚል ድምዳሜ ላይ ደርሷል፡፡ ነገር ግን ከቀድሞ ጥፋቱ እና ቅጣቱ ያልተማረውንም ሰው ቢሆን የቀደመ የወንጀል ሪከርድ እንደ ጠቅላላ የቅጣት ማክበጃ የመጠቀሙ ሁኔታ ገደብ የለሽ እንዳልሆነ ፅሁፉ አሳይቷል፡፡

Published
2023-12-20
How to Cite
ዶ/ር ደጀኔ ግርማ ጃንካ. (2023). የቀደመ የወንጀል ጥፋተኛነት እንደ ጠቅላላ የቅጣት ማክበጃ የሚያገለግልበት ሁኔታ ከኢትዮጵያ የወንጀል ሕግ አንፃር ሲገመገም (Assessment of Prior Criminal Conviction as A General Penalty Aggravating Factor Under the Criminal Code of Ethiopia). Jimma University Journal of Law, 15(1), 1-17. Retrieved from https://journals.ju.edu.et/index.php/jlaw/article/view/5119